Adaretube Large Entertainment Website
Welcome
Login / Register

የኤርትራ የልዑካን ቡድን የሃዋሳን ኢንዱስትሪያል ፓርክን ጎበኘ

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 20 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) የኤርትራ የልዑካን ቡድን የኢትዮጵያን የልማት እንቅስቃሴ ለመመልከት ሃዋሳ ገብቷል።

 በኤርትራው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ዑስማን ሳልህ የተመራው ልዑክና የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ፥ ሃዋሳ ከተማ ሲገቡ በደቡብ ክልል ከፍተኛ ባለስልጣናት አቀባበል ተደርጎለታል።

የልዑካን ቡድኑም በሃዋሳ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ጉብኝት ያደረገ ሲሆን፥ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር በላቸው መኩሪያ ገለጻ ተደርጎለታል።

የልዑካን ቡድኑ ጉብኝት በኢንቨስትመንት መስክ ያለውን ልምድ ለመቅሰም ያለመ ነው ተብሏል።

ኮሚሽነሩ የሃዋሳ ኢንዱስትሪያል ፓርክ በሃገሪቱ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ላይ ተጨባጭ ለውጥ እያመጣ መሆኑንን በዚህ ወቅት ተናግረዋል።

ለዚህም ፓርኩ ወደ ስራ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ ወደ ውጭ ምርቶች በመላክ የውጭ ምንዛሪ ማስገኘት መቻሉን ጠቅሰዋል።

ከዚህ ባለፈም አሁን ላይ ለ18 ሺህ ዜጎች የስራ እድል በመፍጠር ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረጉንም ነው የተናገሩት።

አያይዘውም ኢትዮጵያ በቅርቡ ኤርትራን አንደኛዋ የገበያ መዳረሻ እንደምታደርግም አንስተዋል።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከኤርትራ ጋር ጥላቻ ሳይሆን ሰላምና ፍቅር ያስፈልገናል በማለት የሰላም ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል።

የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂም የሰላም ጥሪውን በመቀበል፥ ከኢትዮጵያ ጋር ገንቢ ውይይት የሚያደርግ የሃገራቸውን ልዑክ በትናንትናው እለት ወደ አዲስ አበባ መላካቸው ይታወሳል።

የልዑካን ቡድኑ በትናንትናው እለት በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የእራት ግብዣ ተደርጎለታል።

 

Related Articles

RSS